የሲቪክ ተቋማት በኢኮኖሚ ልማት፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በግብርና እና ገጠር ልማት፣ የገበያ ጉድለትን በመሙላት ያላቸው ሚና: ከመደመር መፅሐፍ

የሲቪክ ተቋማት በኢኮኖሚ ልማት፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በግብርና እና ገጠር ልማት፣ የገበያ ጉድለትን በመሙላት ያላቸውን ሚና በተመለከተ በመደመር መፅሐፍ የቀረበን ማብራሪያ …..
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር በሚከተለው መልኩ አቅርበውታል።
ሲቪክ ተቋማት
መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሀገራችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑ አሌ አይባልም። በሀገራችን ከሦስት ሺሕ በላይ የተመዘገቡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚገኙ ሲሆን
ከነዚህ ውስጥ ከ235 በላይ የሚሆኑት ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ናቸው። እነዚህ ተቋማት ከሦስት መቶ ሺሕ በላይ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
እነዚህ ተቋማት በአማካኝ በዓመት ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት የሚያንቀሳቅሱ ሲሆን በተለይ በግብርናና ገጠር ልማት እንዲሁም በበጎ አድራጎት ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማበርከት ላይ ይገኛሉ። እነዚህን ተቋማት ትርጉም ባለው መልኩ በማሳተፍ ተደማሪ የልማት ኃይል አድርጎ ማሰለፍ ይቻላል። በተለይም ገበያ ዘለል የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ስለሚያደርጉ በገበያ ጉድለት ምክንያት ለጉስቁልና የሚዳረጉትን ዜጎች የመታደግ ሚና ይኖራቸዋል።
በሀገራችን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የዜጎችን ገቢ በማሳደግ፣ ሥራ አጥነትን በመቀነስ እንዲሁም በአጠቃላይ ማኅበራዊ ፍትሕን በማስፈን በኩል እየተጫወቱት ያለው ሚና ቀላል ባይሆንም፣ ተቋማቱ በአመዛኙ በውጭ ለጋሾች ላይ የተንጠለጠሉ በመሆናቸው የለጋሾችን ፍላጎት የሚያስከብሩ ይሆናሉ፡፡
በተለይም በሕዝብ ስም ተለምኖ ለማኅበራዊ ደኅንነት ሥራ የሚመጣው የዓለም አቀፍ ለጋሾች ገንዘብ፣ ከፊሉ በራሳቸው በለጋሽ ድርጅቶቹ ሰዎችና በዓለም አቀፍ አማካሪዎች እንዲሁም ከእነርሱ ጋር በሚሠሩ ኢትዮጵያውያን ባከኖ ይቀራል። በተጨባጭ ለተጠቃሚዎችና ለአካባቢያዊ ልማት የሚውለው ገንዘብ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
በዚህም ምክንያት የተቋማቱ አስተዋጽዖ ከሚጠበቀው እጅግ ያነሰ ሆኖ ይገኛል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የመንግሥትን የዐቅም ውሱንነት የሚያካከሱ ናቸው። የመንግሥትን አሠራር ለማዘመንና ተጠያቂነትን ለመፍጠር ሚና አላቸው። በተለይም ማኅበራዊ ፍትሕን በማስፈን በኩል ያላቸው ሚና ከፍተኛ ስለሆነ፣ እነሱን በተገቢው መጠን ያላሳተፈና ከእነርሱ ጋር በቂ መናበብ የማይፈጥር የኢኮኖሚ ሥርዓት ጉድለት የሚያጋጥመው ይሆናል::
ከመደመር መፅሐፍ የተወሰደ

