Mon - Fri: 8:30 - 05:30 PM
info@ethiopianchamber.com

Read more

Aug 11, 2025 .

የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ተግዳሮቶችና መሻገሪያ ድልድዮች

         

የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ተግዳሮቶችና መሻገሪያ ድልድዮች:ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ተከታታይ ድርድሮችን እያደረገች ትገኛለች።በአሁኑ ወቅት በድርጅቱ የታዛቢነት ስፍራን በመያዝ ወደ ሙሉ አባልነት ለመቀላቀል እየሠራች ነው። ለመሆኑ የድርጅቱ አባል መሆን በቀጣይ ምን ተስፋና ፈተናዎችን ይዞ ይሆን?

መዚድ ናስር (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ አሶሲየሽን ከፍተኛ አጥኚ እና የንግድና የኢንዱስትሪ ልማት ጥናት መሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የዓለም የንግድ ድርጅት የገበያ ሥርዓት ላይ እክል የሚፈጥሩ የታሪፍና የኮታ ገደብ ተግዳሮቶችን በማስቀረት ነፃ ምህዳር ይፈጠራል። አባል ሀገራቱ ገበያቸውን ክፍት እንዲያደርጉና እርስ በእርስ እንዲገበያዩ ድርድር የሚያደርጉበት መድረክ ነው። በእዚህ መደረክ ሀገራት ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ በመላክና ሀገር ውስጥ በማስገባት ጥቅማቸውን ለማሳደግ የሚሠሩበት እንደሆነ ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ ወደ ድርጅቱ ተቀላቅላ ገበያውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ክፍት ብታደርግ የተቀላጠፈ የንግድ ልውውጥ እንዲኖር ይረዳል። ዜጎችም የተለያዩ ምርቶችን በዝቅተኛ ዋጋ ማግኘት ይችላሉ።

‹‹የዓለም የንግድ ደርጅት አባል መሆን አያሌ ጥቅሞች አሉት። እነዚህን ጥቅሞች በላቀ ደረጃ ለኢትዮጵያ እድገት ለመጠቀም የመደራደር አቅማችን ከፍ ሊል ይገባል። በተለይ ምርቶች በብዛት ወደሚላክባቸው ሀገሮች ገበያ በነፃነት ለመግባት ጥቅም ይሰጣል›› የሚሉት መዚድ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በአንፃራዊነት ወደ አውሮፓ ህብረት፣ ወደ አሜሪካ ወደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬት፣ ሳውዲ አረቢያ ምርቶቿን በብዛት እንደምትልክ ያነሳሉ። በተቃራኒው ቻይናን ከመሰሉ ሀገራት የምታስገባቸው ምርቶች ከምትልከው አንፃር ብዛት ያለው መሆኑን ያስረዳሉ።

‹‹ለአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የምንልከው ምርት 25 በመቶ አካባቢ ነው። ወደ ሀገር ውስጥ የምናስገባው ደግሞ 10 በመቶ ነው›› በማለትም፤ በእዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ በዝቅተኛ ታሪፍ ምርቶችን መላክ ከተቻለ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ይረዳል ይላሉ። በእዚህ ምክንያት የድርጅቱ አባል መሆን ኢትዮጵያ ምርቶቿን በብዛት ወደምትልክባቸው ሀገራት በነፃ የገበያ ሥርዓት በመዳኘት የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ያስችላታል።

የዓለም የንግድ ደርጅት አባል ለመሆን መንግሥት አሁን ከሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንፃር ተመጋጋቢ ጥቅሞች ነው ያሉት የሚሉት መዚድ (ዶ/ር) ፤ በተለይ ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ በተፈጥሮ የበለፀጉ የግብርና ምርቶችን ወደ አውሮፓ ገበያ ማስገባት የምትችልበት መንገድ ከተመቻቸ ተጠቃሚ ትሆናለች። ለእዚህም የሁለትዮሽ የመደራደር አቅምን ማሳደግ ይገባል ይላሉ።

‹‹ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ስትሆን የመንግሥት ገቢ ይቀንሳል›› የሚሉት መዚድ ናስር (ዶ/ር)፤ ይህ በፍጥነት ሊታዩ ከሚችሉ ተግዳሮቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ያስረዳሉ። በሁለተኛነት፤ መንግሥት ገበያውን ክፍት ሲያደርግ ከሚያጣቸው ነገሮች አንዱ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ነው። ለምሳሌ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚለውን የመንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫ እና ኢንዱስትሪዎች ምርታማ እንዲሆኑ የሚደረግ ንቅናቄ ማየት ይቻላል። በዓለም የንግድ ድርጅት በሚደረግ ድርድር ውስጥ የኢንዱስትሪ ምርቶች በዝቅተኛ ታሪፍ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ከተደረገ እና ገበያ ውስጥ ከተሰራጨ አምራቾች አሁን ባላቸው የማምረት አቅም መወዳደር ስለማይችሉ ተወዳዳሪ ሆነው መውጣት ያዳግታቸዋል። በመሆኑም ኢንዱስትሪዎች በእዚህ ሂደት ውስጥ ተጎጂ እንዳይሆኑ እና ከውድድር እንዳይወጡ መንግሥት በድርድሩ ላይ ጫና ማድረግ ይኖርበታል ይላሉ።

መዚድ ናስር (ዶ/ር) አባል ከመሆን ጋር ተያይዘው ሊመጡ ከሚችሉ አሉታዊ ጎኖች መካከል፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የታሪፍ መጠንን መቀነስ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህ ሲሆን መንግሥት ቀደም ሲል የሚያገኛቸው ገቢዎች ሊቀንሱ እንደሚችሉ ያስረዳሉ። በረጅም ጊዜ ደግሞ በሀገር ውስጥ ያሉ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች ተወዳዳሪነታቸው ከፍ ካላለ ሊዳከሙና ከገበያ ሊወጡ ይችላሉ የሚል ሃሳብ ያስቀምጣሉ። በመሆኑም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ጥንቃቄ ሊወሰድ ይገባል ሲሉ ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ።

የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው ሌላኛው እንግዳ ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) ናቸው። እርሳቸው አባልነቱ ምርቶችን አባል ወደሆኑት ሀገራት ገበያ ለማስገባትና ተወዳዳሪ ለመሆን ጠቀሜታ አለው ይላሉ። ሂደቱም የኢትዮጵያን የገበያ አማራጮች ለማስፋት ይረዳል ብለዋል።

‹‹አባል ሀገራት በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ መረጃን በነፃነት ያገኛሉ። የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግርም እንዲሁ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል›› የሚሉት ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር)፤ አባል መሆን በተለይ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ላይ ኢኮኖሚያቸውን ለገነቡ ሀገራት የተሻለ ጥቅም ይሰጣል ይላሉ። ይህንን መሰል ሽግግር ለማድረግ ሲታሰብ የሰለጠነ የሰው ሃይል፣ ምቹ ሕግና የአሠራር ሥርዓት እንደሚጠይቅም አፅእኖት ይሰጣሉ። በእዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ዝግጅቶችን በማድረግ አባል ከመሆን የሚገኙ ጥቅሞችን በተሻለ ቁመና ለማግኘት መሥራት ይኖርባታል ሲሉ ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ።

የድርጅቱ አባል ከመሆን ጋር የሚነሱ ተግዳሮቶች ጋር ተያይዞ በሚነሱ ጉዳዮች መዚድ ናስር (ዶ/ር)፤ ያነሷቸውን ሃሳቦችን ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) ይጋሯቸዋል። በተለይ ትላልቅ ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅቶች ሀገር ውስጥ ገብተው ሲሠሩ አምራቾች ተወዳዳሪ ባልሆኑበት ሁኔታ በቀላሉ ከገበያ እንዳይወጡ ያሰጋል ይላሉ። በመሆኑም የሀገር ውስጥ አምራቾች እና አገልግሎት ሰጪዎች አቅም መጎልበት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል በማለት ይመክራሉ።

‹‹ተወዳዳሪ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች እና አምራቾችን መፍጠር ካልተቻለ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በውጭ ሀገራት ድርጅቶች ላይ ጥገኛ ይሆናል›› የሚል ስጋት ያላቸው አለማየሁ (ዶ/ር) የኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያን ተሞክሮ በማንሳት ሀገር በቀል ያልሆኑ ድርጅቶች ሊበዙ ይችላሉ ይላሉ። ይህንን ስጋት መቀልበስ የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባም ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ መንግሥት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሚያስችል ቁመና ላይ እንገኛለን የሚል አቋም ይዟል። ከድርጅቱ ጋር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተከታታይ ድርድሮችንም እያካሄደ ነው። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ነው፤ ጂዲፒው በዓመት 8 ነጥብ 4 በመቶ እያደገ ነው። ከሁለትና ሶስት ዓመት በኋላ ከታዳጊ ሀገሮች (LDC) ተርታ እንወጣለን በማለት፤ ከእዚህ ተርታ መውጣት ድርድሩን እንደ አዲስ እንዲጀመር ከማስገደዱም ባሻገር ኢትዮጵያ በጊዜ አባል በመሆን የምታገኛቸውን ጥቅሞች እንደሚያሳጣ በማንሳት ጊዜው አሁን እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል የመሆን ሂደት 23 ዓመታትን የፈጀ ሲሆን ከታዛቢነት በመውጣት በቀጣይ የፈረንጆች ዓመት በ2026 መጋቢት ወር ላይ ከፍፃሜ ለማድረስ እየተሠራ እንደሆነ ታውቋል። (ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተወሰደ)

 

 

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Ethiopian Chamber of Commerce and Sectoral Associations

Contact Info

Mon - Fri : 8:00 AM - 05:00 PM
Sat : 8:00 - 06:00 PM
+251 115 514 005
info@ethiopianchamber.com
+251-115-517699
517

Office Address

Mexico Square, Addis Ababa, Ethiopia