የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ልቆ የሚታይበት 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ:- እኤአ ከመስከረም 8 እስከ 10 ቀን 2025 በአዲስ አበባ
የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ልቆ የሚታይበት 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ
በኢትዮጵያ መንግስት እና በአፍሪካ ህብረት አዘጋጅት የሚካሄደው 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ (Second Africa Climate Summit (Acs2)) በአዓለም አቀፍ ደረጃ ከ25 ሺ በላይ ተሳታፊዎችን በማሳተፍ ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡
የመጀመሪያው የአየር ንብረት ጉባኤ በኬንያ ናይሮቢ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከመስከረም 4 እስከ 6 ቀን 2023 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን Driving Green Growth and Climate Finance Solutions for Africa and the World” በሚል መሪ ቃል ነበር የተካሄደው፡፡
በዚህ ጉባኤም በርካታ የአፍሪካ መንግስታት፣ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የአየር ንብረት ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል፡፡
በወቅቱም ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ከ20 ቢሊየን ዶላር በላይ ቃል የተገባ ሲሆን በአየር ንብረት ለውጥ እና በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ የናይሮቢ ዲክላሬሽን ሰነድ መዘጋጀቱም ይታወሳል፡፡
ከቀናት በኋላ በአዲስ አበባ በሚካሄደው 2ኛው ጉባኤ ደግሞ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች ከተለያዩ አደረጃጀቶች የሚሰባሰቡ የአየር ንብረት ለውጥ አክቲቪስቶች እና በርካታ እንግዶች ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡
ይህ ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና መፍትሄ ለመፈለግ ወሳኝ ጉባኤ ሲሆን ኢትዮጵያም በዘርፉ የምታደርገውን የላቀ አስተዋጽኦ የምታሳይበት እንዲሁም የአፍሪካ ሀገራት ተሳታፊዎች በጋራ የሚመክሩበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
እኤአ ከመስከረም 8 እስከ 10 ቀን 2025 በአዲስ አበባ በሚካሄደው ጉባኤ ኢትዮጵያ ያሏትን ተሞክሮዎች የምታካፍልበት፣ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሞክሮ የሚለዋወጡበት እንዲሁም ከዋና ጉባኤው ጎን ለጎንም የጎንዮሽ ውይይች እና ምክክሮች የሚደረጉበት ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በተካሄዱት የዓለም አቀፍ የኮፕ ጉባኤዎች ያሏትን ተሞክሮዎች እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ መዛባትን ለመከላከል እየወሰደችው ያለውን እርምጃ ማጋራቷ የሚታወስ ሲሆን በተለይም ከታዳሽ ኃይል አጠቃቀም ጋር በተያየዘ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የኤሌክትሪክ ኀይልም ከታዳሽ ኃይል መሆኑ በአርዓያነት የሚወሰድ ነው፡፡
በዚህ ጉባኤ ከ100 በላይ ተናጋሪዎች በጉዳዩ ዙሪያ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን ከ25 ሺ በላይ ልዑካንና ተሳታፊዎች ይታደማሉ፡፡ለእንግዶች እና ለተሳታፊዎችም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መልዕታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
“Ethiopia, the Land of Origins, in collaboration with the African Union, is deeply honored to welcome you to the Second Africa Climate Summit (ACS2), taking place from September 8–10, 2025. This landmark gathering offers a vital opportunity to redefine Africa’s aspirations for a climate-resilient and prosperous future …” Abiy Ahmed Ali (prime minister, FDRE)
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍሪካውያን የአጀንዳ 2063 መርህ የሆነውን ብዝሀነትን በማጉላት የአህጉሩን አረንጓዴ ልማት ማፋጠን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

“Accelerating Global Climate Solutions: Financing For Africa’s Resilient And Green Development”
የአፍሪካን ዘላቂ የአረንጓዴ ልማት ፋይናንስ በማድረግና በመደገፍ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ መሻት ዋነኛው የጉባኤው መሪ ሀሳብ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ኮንቬንሽን ማዕከል በሚካሄደው 2ኛው ጉባኤም የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎች፣ የልማት ባንኮች፣ በጎ አድራጎት ተቋማት፣ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችና ባለሀብቶች እንደሚሳተፉና ውጤታማ ጉባኤ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከዋናው ጉባኤ መካሄድ ቀደም ብሎ እኤአ ከመስከረም 5 እስከ 7 ቀን 2025 የቅድመ ጉባኤ ዝግጅቶቸ በደማቅ ሁኔታ እንደሚካሄድ ከወጣው መርሀ ግብር ማወቅ ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት በጉባኤው ድረ ገጽ በመመዝገብ እንዲሁም ከእንግዳ አቀባበል ጀምሮ የላቀ ተሳትፎ በማድረግ ኢትዮጵያዊ ወግና ባህሉን ማሳየት እና ለጉባኤው ስኬት መሳካት የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያስገነዝባል፡፡

የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች እና ማኅበራት፣ ባለሀብቶች፣ የሆቴል ባለቤቶች፣ የትራንስርት ባለንብረቶች እና በተለያየ መልኩ እንግዶችን የሚያስተናግዱ አካላት የላቀ ተሳትፎ በማድረግ እና ለእንግዶች አስፈላጊውን አገልግሎት በመስጠት፣ በሚካሄዱ የጎንዮሽ ውይይቶች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ እና የኢትዮጵያን መልክ በማስተዋወቅና በአግባቡ በማስረዳት ረገድ ኃላፊነትን መወጣት አስፈላጊ ነው፡፡
በሌላ በኩል የኮንፍረንስ ቱሪዝምን በማሳደግ ረገድ አስፈላጊ ምርትና አገልግሎቶችን በአግባቡ በማቅረብ የጉባኤው ተሳታፊዎች ስለ ኢትዮጵያ መልካም ግንዛቤ እንዲኖራቸው እንዲሁም ምርትና አገልግሎትን በማስተዋወቅ ትልቅ ስራ መስራት ይጠበቃል፡፡
በኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ጋር በተያያዘ የቴክሎጂ፣ የአመራረት እንዲሁም በበርካታ ዘርፎች ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ፣ ምርትና አገልግሎቶች እንዲተዋወቁ ማስቻል፣ ቀጣይነት ያለው ትስስር እና የቢዝነስ ግንኙነት መፍጠር፣ በአረንጓዴ ልማት ዘላቂነት ያለው የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ለማስረጽ እና ለማረጋገጥ ሁለተኛው የአየር ንብረት ጉባኤ ትልቅ እድል ይዞ የሚመጣ በመሆኑ ከጉባኤው ትልቅ ውጤት እንደሚገኝ ይታመናል፡፡
ስለሆነም በጉባኤው ድረ ገጽ www.africaclimatesummit2.et በቀጥታ በመመዝገብ ተሳታፊነትን ከወዲሁ ማረጋገጥ እንደሚገባ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም በቅድመ ጉባኤ እና በጉባኤው ሂደት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ ያረጋግጣል፡፡

