ኢትዮጵያና ሳውዲ አረቢያ በዲፕሎማሲና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጠንካራ ወዳጅነት አላቸው፡- አቶ ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር

ኢትዮጵያና ሳውዲ አረቢያ በዲፕሎማሲና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጠንካራ ወዳጅነት አላቸው፡-
አቶ ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር ይህንን ያሉት በአዲስ አበባ ማሪዮት ሆቴል በተካሄደው የኢትዮ- ሳዑዲ የቢዝነስ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
ለአመታት የቆየው የሁለቱ አገራት ግንኙነትም በንግድ፤ በኢንቨስትመንት፣ በኢንዱስትሪ እና በቱሪዝም ዘርፎችም ከጊዜ ወደጊዜ የበለጠ እየተጠናከረ የመጣ መሆኑንም አቶ ሰብስብ አስረድተዋል፡፡

በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር እንዲረዳ፤ የአገራቱ የንግድ ምክር ቤቶች የጋራ የንግድ ካውንስል የመሰረቱ ሲሆን፤ ዓላማውም ሁለቱም አገራት የንግድ መረጃ ልውውጥን እንዲያጎለብቱ፤ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ዕድሎች የሁለቱን አገራት ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲጠቀሙ ለማገዝ፣ የስራ ፈጠራን ሊያበረታቱ እና ምርቶችን እና አገልግሎቶችን ሊያስተዋወቁ የሚችሉ ኤግዚቢሽኖችን በጋራ ለማካሄድ እንዲሁም ንግድ ለንግድ ውይይቶች የሚጠናከሩበትን መደላድል ለመፍጠር ነው ብለዋል አቶ ሰብስብ።
ኢትዮጵያ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ መልካም ዕድሎች ያላት አገር እና ልዩ የመልማት አቅም፣ ሰፊ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል፤ ምቹ የህግ ማዕቀፍ እንዲሁም በመንግስት በኩል አስፈላጊ የሆኑ የድጋፍ ሁኔታዎች ያሉ መሆኑን በመግለጽ፣ የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶችም ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በግል ወይም በጋራ ከኢትዮጵያ ባለሃብቶች ጋር ማልማት እንዲችሉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

