በማዕድን እድሎች እንዲሁም በዘርፉ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።


በማዕድን እድሎች እንዲሁም በዘርፉ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።
(ECCSA:16/4/2018 ዓ.ም)
በማዕድን ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት እንዲሁም በሳይፕ( Center for International Private Enterprises) ትብብር በተዘጋጀው ውይይት ላይ ከተለየዩ ክልልሎች የተውጣጡ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤቶች አመራሮች እና የማዕድን ቢሮ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን በኢትዮጵያ ባሉ የማዕድን ሀብት እድሎች እንዲሁም ዘርፉን ለማልማት መወሠድ ያለባቸው ጉዳዮች በባለድርሻ አካላት ተነሥተዋል።
የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ብርሃኔ ያደሳ የውይይት መድረኩ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ያገናኘ እና ለቀጣይ መሠረት የጣለ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ በቂ መረጃ ለሚመለከታቸው አካላት ለማድረሥ እየሠራ ሲሆን በተለይም ዲጂታል ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተው ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሠሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

MINTEX ኤክስፖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን፣ በቀጣይም በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ ለማዘጋጀት እቅድ እንዳለና ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት አንዱ ባለድርሻ መሆኑን ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት የቦርድ አባል መጋቢ ሥርዓት ቀሲስ ታዬ ለታ ሁሉም ተባብሮ መሥራት እንዳለበትና የምክር ቤቶች ትልቁ ሥራም የሀገሪቱን ምርትና አገልግሎቶች ማሥተዋወቅና የግሉ ዘርፍና የመንግስት አገናኝ ድልድይ መሆናቸውን ተናግረዋል፣
በመሆኑም የማዕድን ዘርፉን በትብብር ለማልማት ትልቁን ሚና መጫዎት እንደሚገባቸው ያነሱት መጋቢ ሥርዓት ታየ ሠላምን በማረጋገጥ ለማዕድን ልማት እድገትና ተጠቃሚነት እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ የማዕድን ሀብቶች የበለጸገች እና ሠፊ የሀብት ባለቤት ብትሆንም ዘርፉ በአግባቡ ባለመልማቱ ማኀበረሠባዊ ተጠቃሚነት ግን አሁንም ከሚጠበቀው በታች ነው።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ ( ተባባሪ ፕሮፌሠር) በበኩላቸው ቀጣይነት ባለው መልኩ ምክር ቤቱ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመሆን በቅርበት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

በምክር ቤቱ የቢዝነስ አመራር አካዳሚ በኩል በተለይም በአካባቢ ጥበቃ እና በማዕድን ሥራው ዙሪያ የአቅም ግንባታ ሥራን አጠናክሮ እንደሚሠራ ገልጸው ከክልል የማዕድን ቢሮዎችና እንደ ሳይፕ ካሉ የልማት አጋሮች ጋርም በትብብር እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ከጥር 27-የካቲት 1/2018 ዓ.ም በሚካሄደው 15ኛው ኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢትም ከሚተዋወቁ ምርቶች አንዱ ማዕድን በመሆኑ በዘርፉ የተሠማሩ አካላት እንዲሳተፉ ዶክተር ቀነኒሳ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በዘርፉ ለሚሠማሩ አልሚዎች እየተሠጡ ባሉ ድጋፎች፣ በሰላምና ጸጥታ መሥተካከል እንዲሁም በማሽነሪ አቅርቦት፣ በጥራት ቁጥጥርና ከትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በትብብር መሥራት በሚቻልባቸው አግባቦች ዙሪያ አስተያየቶች ተሠጥተዋል።
በማዕድን ማምረት ሂደት የአካበቢውን ማኀበረሠብ ባሣተፈ መልኩ መሥራት እንደሚገባም በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
በሥራ እድል ፈጠራ በተለይም ከፍተኛ አምራቾችን ብቻ ሣይሆን አነስተኛ እና መካከለኛ አምራቾችን ለማሣተፍ እና አሥፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ተጠቁሟል።

