የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የማኔጅመንት አባላት ከኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱትሪ ማህበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ጋር ተወያየ፡፡

በዋና ፀሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) የተመራው የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የማኔጅመንት አባላት ከኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱትሪ ማህበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ጋር ተወያየ፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እራሱን በአዲስ መልክ ካደራጀና መዋቅራዊ ሪፎርም ካካሄደ ወዲህ ከአባላቶቹ ጋር ያለውን የስራ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ተቀራርቦ መስራት መጀመሩን የገለፁት ወና ፀሐፊው ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ፤ አባሎቻችን ከሆኑት የዘርፍ ማህበራት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ ማህበር ጉብኝት እና የምክክር ዓለማም ይሄው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በቀጣይ ሁለት የስትራቴጂክ ዓመታት ውስጥ የግሉ ዘርፍ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የመሪነት ስፍራ እንዲኖረው ምቹ ምህዳርን ለመፍጠር ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የግሉ ዘርፍም አለማአቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ እራሱን ከወቅቱ ጋር እያጣጣመ በመሄድ ለሚጠብቀው ብርቱ ፉክክር እራሱን ማዘጋጀት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዘላለም መርኣዊ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የቆዳ ዘርፍ ያሉበትን በርካታ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞና ምቹ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመጠቀም በአለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ እየሆነ መመምጣቱን ጠቁመው፤ በተለይም በአፍሪካ ደረጃ ግንባር ቀደም እንደመሆኑ አሁን በተከፈተው የአፍሪካ ነፃ አህጉራዊ የንግድ ቀጠና ውስጥ በሰፊው ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውንና ለዚህም ከኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር ተቀራርቦና ተቀናጅቶ መስራት እንደሚፈልጉ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ ዳኛቸው አበበ የማህበሩን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ፣ ያሉበትን ችግሮችንና የዘርፉን ምቹ ሁኔታዎች አስረድተዋል፡፡
ማህበሩ ከ200 በላይ አባላት ያሉት ሲሆን የቆዳ እና የጫማ ፋብሪካዎች እንዲሁም የፋብሪካዎቹ ግብዓት አቅራቢዎችን በአባልነት የያዘ ነው፡፡

