ኢትዮጵያ እና ጃፓን በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ተወያዩ

ኢትዮጵያ እና ጃፓን በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ተወያዩ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኩኒሚትሱ አያኖ ከተመራ የንግድ እና ኢንቨስትመንት የልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ከ35 በላይ የጃፓን ኩባንያዎች ለተውጣጡ 48 የቢዝነስ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ስላለው አዲስ እና ምቹ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ገለጻ አድርገዋል። ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

ሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው የገለጽት ሚኒስትሩ፤ በሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን የግንኙነት መድረኮችም ጠንካራ ትብብር እንዳላቸው አንስተዋል።
ጃፓን ለኢትዮጵያ ለምታደርጋቸው የልማት ድጋፎች ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በንግድ እና ኢንቨስትመንት እየተሻሻለ የመጣው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የበለጠ መጠናከር እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኩኒሚትሱ አያኖ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ እና ጃፓን ግንኙነት በንግድ እና ኢንቨስትመንት የበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አንስተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ለልዑካን ቡድናቸው ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው፤ ነገ በሚካሄደው የኢትዮ-ጃፓን ቢዝነስ ፎረም እንደሚሳተፉ ጠቁመወል።
ፎረሙ የሁለቱን ሀገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር ረገድ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረውም ተገልጿል።

