ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በኢንዱስትሪ መካከል ያለዉን ትስስር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከደብረብርሃን ዪኒቨርሳቲ አመራሮች ጋር መክረዋል።


የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በኢንዱስትሪ መካከል ያለዉን ትስስር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከደብረብርሃን ዪኒቨርሳቲ አመራሮች ጋር መክረዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በየዓመቱ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሚያስመርቋቸዉ ወጣቶችና ኢንዱስትሪዎች በተጨባጭ የሚፈልጉት የሰዉ ኃይል የተጣጣመ እንዲሆን አምራች የሰዉ ኃይልን የሚያፈሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የተፈራዉን የሰዉ ኃይል ወደ ተግባራዊ ስራ የሚያስገባዉ አምራች ኢንዱስትሪዉ ተቀራርበዉና ተቀናጅተዉ መስራት እንዳለባቸዉ ዶ/ር ቀነኒሳ በአፅንኦት ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ የግሉ ዘርፍ ድምፅ ከሆነዉ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ተቀናጅቶ በመስራት የግሉን ዘርፍ ወይም የኢንዱስትሪዉን ዘርፍ በጥናት በመለየት የታዩ ክፈተቶችን ሊሞላ የሚችል የሰዉ ኃይል በማፍራት ላይ አትኩሮ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲዉ አመራሮችና መምህራኖች በበኩላቸዉ አሁን ያሉት የትምህርት ክፍሎች የሚሰጧቸዉ ስልጠናዎች እንደተለመደዉ በቲዮሪ ላይ ብቻ የተመረተ ሳይሆን በተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ የኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም ኢንዱስትሪዎች የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ከቀጠሩ በኋላ ከኢንዱስትሪዉ ጋር ለማላመድ ተጨማሪ ስልጠናዎችን ለመስጠት የሚያባክኑትን ጊዜና ገንዘብ ለማስቀረት ያስችላል ብለዋል።

