ለመደመር መንግሥት አዲሱ ካቢኔ እና ተሿሚ ሚኒስትሮች እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እወዳለሁ – የተከበሩ ሰብስብ አባፊራ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሊ (ዶ/ር) የመደመር መንግሥት ካቢኔያቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው አፀድቀዋል።
በመሆኑም ዛሬ ስራ ለጀመረው አዲሱ ካቢኔ እና ተሿሚ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ በመላው የንግዱ ማኅበረሰብ እንዲሁም በራሴ ስም እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እወዳለሁ።
በአገራችን እየተካሄዱ ያሉ መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ወደ ተጨባጭ የንግድ እድሎች፣ የኢንቨስትመንት፣ የምርት አቅም እና የወጪ ንግድ ውጤቶች መቀየር የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት ነው።
በዚህ ረገድ፤ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በተናጠል ሳይሆን በተቀናጀ መንገድ መስራታቸው ወሳኝ መሆኑ ያለፋት ውጤቶቻችን ምስክሮች ሲሆኑ፤ በይበልጥም ፤ የግሉ ዘርፍ የሚያጋጥሙትን የፖሊሲ፣ የተቋማት ቅንጅት፣ የፋይናንስ፣ የሎጂስቲክስ፣ የግብዓት እና የገበያ ችግሮች በቀጣይነት በመወያየትና በጋራ መፍትሔ በመፈለግ የንግድ ስራ አካባቢውን በቀጣይነት ከዚህም በላይ ማሻሻል ከሁላችንም የሚጠበቅ ቀጣይ ተግባራችን ይሆናል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም፣ ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትንና ፍትሐዊ የንግድ አሠራርን ማስፈን የተሻለ የንግድ አካባቢ ለመፍጠር መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ስለሆነም ሙስናንና ማንኛውንም የብልሹ አሠራር ተግባር በጋራ በመከላከልና በመታገል፣ የሕግ የበላይነትን፣ ፍትሐዊ ውድድርንና ታማኝነትን በንግድ ስርዓቱ ውስጥ ማጠናከር ይገባል።
ይህም የግሉ ዘርፍ የሚገባውን የኢኮኖሚ አስተዋፅዖ በሙሉ እንዲያበረክት ከማድረጉም በላይ የባለሀብቶችንና የንግዱን ማኅበረሰብ እምነት ለማጠናከር ወሳኝ ነው።
የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ የተሳታፊ ብቻ ሳይሆን የእድገት ዋና አጋር ነው። ስለዚህም የንግድና ዘርፍ ማኅበራትን ጨምሮ መላው የንግዱን ማኅበረሰብ የሚያካትት፣ በማስረጃና በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ ውይይት ይበልጥ ማጠናከር ይኖርብናል።
ኢትዮጵያ ያላትን የሰፊ የሀገር ውስጥ ገበያ፣ የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ሀብትና የክልላዊ እና ዓለም አቀፍ ገበያ ትስስር በተሻለ መልኩ መጠቀም ከተቻለ በምርት፣ በኢንቨስትመንት፣ በወጪ ንግድና በሥራ ፈጠራ የሚገኙ እድሎች በእጅጉ የሚሰፉ ይሆናሉ። ለዚህም የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከየሚመለከታቸው የሚኒስቴር መ/ቤቶች ጋር እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ አብሮ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት ያረጋግጣል።
ምክር ቤታችን በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል የፖሊሲ ውይይትን በማጠናከር፣ የንግድ ማኅበረሰቡን ጥያቄና ምክረ ሀሳብ በማቅረብ እና የጋራ አጀንዳዎችን በማስፈፀም ረገድ ከእናንተ ጋር በቅርበት ለመስራት ዝግጁ ነው።
አዲሱ ኃላፊነታችሁ በተጨባጭ ውጤት፣ በተቋማዊ ትብብር እና በሕዝብና በንግዱ ማኅበረሰብ እምነት የሚገለጽ የስኬት ጉዞ እንዲሆን እመኛለሁ።
የተከበሩ ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት
