ለአለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር 6ኛው የስራ ቡድን ስብሰባ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ የተገኘው የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን ከአርጀንቲና ሪፐብሊክ ቋሚ ተልዕኮ አምባሳደር ጉስታቮ ሉናዚ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አደረገ፡፡

ለአለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር 6ኛው የስራ ቡድን ስብሰባ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ የተገኘው የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን ከአርጀንቲና ሪፐብሊክ ቋሚ ተልዕኮ አምባሳደር ጉስታቮ ሉናዚ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አደረገ፡፡
በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ በአለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ድርድር ሂደት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የሆነውን ከአርጀንቲና ጋር ያላትን የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድር በቴክኒክ ደረጃ በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቋን የኢትጵያ ዋና ተደራዳሪ እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) አረጋግጠዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲሁም በግብርና፣ በንግድ፣ በቴክኖሎጂ፣ በአቬሽንና በቱሪዝም ዘርፎች ያላቸውን ሰፊ ትብብርና አቅም ዶ/ር ካሳሁን አጉልተው አሳይተዋል፡፡

በአለም ንግድ ድርጅት በቅርቡ በተካሄደው 14ኛው የሚኒስትሮች ኮንፈረንስ መሰረት በተቀመጠው የድርድር ፍኖተ ካርታ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገንና በሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድሮች ከፍተኛ እድገት ማስመዝገቧን የገለጹት ሚኒስትሩ በቴክኒክ ደረጃ የተጠናቀቁ ስምምነቶች በፊርማ እንዲያልቁ መደረጉ ለሂደቱ ያለውን ጠቀሜታም አጽንኦት ሰጥተውታል።
አምባሳደር ሉናዚ በበኩላቸው አርጀንቲና ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን እንድትቀላቀል ሙሉ ድጋፍ እንደምትሰጥ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በቴክኒክ ደረጃ የተጠናቀቀውን የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድር ለመፈረም የሚያስፈልገውን ሂደት ለማፋጠን እንደሚሰሩ ቃል ገብተው አርጀንቲና ከኢትዮጵያ ጋር በብዙ ዘርፎች በጠንካራ ትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላትም ገልጸዋል።
Source – MOTRI

