“የሎጂስቲክስ አቅርቦት ለቀጣናዊ የቢዝነስ ትስስር” በሚል መሪ ሐሳብ ሁለተኛው የኢትዮ ጂቡቲ የቢዝነስ ማስፋፊያ ጉባዔ በጂቡቲ እየተካሄደ ነው።

2ኛው የኢትዮ ጂቡቲ የቢዝነስ ማስፋፊያ ጉባዔ እየተካሄደ ነው::
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) “የሎጂስቲክስ አቅርቦት ለቀጣናዊ የቢዝነስ ትስስር” በሚል መሪ ሐሳብ ሁለተኛው የኢትዮ ጂቡቲ የቢዝነስ ማስፋፊያ ጉባዔ በጂቡቲ እየተካሄደ ነው።
ጉባዔው የኢትዮጵያ እና ጂቡቲን የሎጂስቲክስ ትብብር ለማሳደግ ያለመ ሲሆን÷ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማሕበራት ም/ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አይናለም አባይነህ (ዶ/ር)፣ የጅቡቲ ንግድና ቱሪዝም ሚኒስትር ሞሀመድ ዋርሳማ ዲሬህ እና የዘርፉ ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ ዘርፍ ማሕበር ፕሬዚዳንት ኤልሳቤት ጌታሁን ጉባዔው በሎጂስቲክስ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ቀጣይነት ያለውን የቢዝነስ ዕድገት ለማፋጠን እንደሚረዳ ተናግረዋል።
ጉባዔው ለእድገትና ትራንስፎርሜሽን በሚፈጥረው ዕድል ለቀጣናው ተምሳሌታዊ ትብብር እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

የጂቡቲ የንግድና ቱሪዝም ሚኒስትር ሞሀመድ ዋርሳማ ዲሬህ በበኩላቸው÷ ጉባዔው የሁለቱን ሀገራት የንግድ ትብብር በማሳደግ የኢትዮ ጂቡቲ ኮሪደርን ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የትስስር፣ የዕውቀት ሽግግር እና ስትራቴጂካዊ ትብብር ለመፍጠር የሚያስችል መድረክ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በመድረኩ የሎጂስቲክስ ዘርፉን አቅም ለማሳደግ መሰል ትብብሮች ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተጠቅሷል።
ጉባዔውን የኢትዮ ሎጂስቲክስ ዘርፍ ማሕበር ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት፣ ከጂቡቲ ንግድ ምክር ቤት እና ትሬድ ማርክ አፍሪካ ጋር በመተባበር ማዘጋጀታቸው ተገልጿል።
የቀጣናውን ሀገራት የሎጂስቲክስ ንግድ ትስስር ለማጠናከር ያለመው የመጀመሪያው ዙር መድረክ አዲስ አበባ ተካሂዷል።

