የሲዳማ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በላከልን መረጃ ሲዳማ ቻምበር 3ኛውን የመንግሥት እና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ (PPD) አካሂዷል ።


የሲዳማ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በላከልን መረጃ ሲዳማ ቻምበር 3ኛውን የመንግሥት እና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ (PPD) አካሂዷል ።
የሲዳማ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከCIPE (Center of International Private Enterprise) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሦስተኛው የመንግሥትና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ (PPD) በሐዋሳ ከተማ በከፍተኛ ድምቀትና ተሳትፎ ተካሄዷል።
መድረኩን የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ የእንኳን ደህና መጣችሁ መክፈቻ ንግግር በማድረግ በይፋ የከፈቱት ሲሆን፤ መንግሥትንና የግሉን ዘርፍ በአንድ ማዕድ በማሰባሰብ የንግድ ማኅበረሰቡን ችግሮች በመቅረፍ ረገድ መድረኩ ያላቸውን ትልቅ ፋይዳ አንስተዋል።
ይህ መድረክ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ማኅበር ሦስተኛው ብሔራዊ የንግድ አጀንዳ ልየታ መሠረት ለሲዳማ ክልል ንግድ ማኅበረሰብ በዋና ማነቆነት የታዩትን ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች መካከልም ግብር እና ጉምሩክ እና የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት ይገኙበታል።

በዕለቱ ከነጋዴዎች ተጨማሪ ግብዓቶች ተሰብስበው በጥናት ግኝት መልክ የቀረቡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም በሥራቸው ላይ ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች በማንሳት ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በግብርና ጉምሩክ ጉዳይ፦የፌዴራል ገቢዎች ባለሥልጣን ሐዋሳ ቅርንጫፍ ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞሐመድ አዎል በመድረኩ ተገኝተው በግብር አስተዳደርና አሰራር ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች በጥልቀት፣ በዕውቀት እና በልምድ የታገዘ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፤ እንዲሁም በቅንጅት የሚሠሩ የቤት ሥራዎችን በባለቤትነት ተቀብለዋል።
እንዲሁም በፋይናንስና ብድር አቅርቦት ጉዳይ፦ነጋዴዎች የኮላተራል (መያዣ) እጥረት እና ብድሩን በፈለጉት ጊዜ ውስጥ ባለማግኘት ሥራቸው ላይ ፈተና እንደፈጠረባቸው አንስተዋል። በበኩላቸው በመድረኩ የተገኙት የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎች፤ ዋና ሥራቸው ብድር ማቅረብ መሆኑን በመጥቀስ አሁን ላይ በብሔራዊ ባንክ በኩል የተደረጉ ማሻሻያዎችን መሠረት አድርገው የተቀላጠፈ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አብራርተዋል፤ ከንግድ ምክር ቤቱ ጋርም በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለንግድ ማኅበረሰቡ መሻሻል በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ከፌዴራል እስከ ከተማ አስተዳደር ያሉ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ ተወካዮች፣ ላኪዎች፣ አስመጭዎች እና ነጋዴዎች በንቃት የተሳተፉበት ውይይት ፍሬያማ ሆኖ ተጠናቋል።

