የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት (ECCSA) ምክትል ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ሔለን ረታ በሐዋሳ ከተማ የሚገኘውን ፊኒስ የጤፍ ዱቄት ማቀነባበሪያ ፋብሪካን ጎበኙ።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት (ECCSA) ምክትል ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ሔለን ረታ በሐዋሳ ከተማ የሚገኘውን ፊኒስ የጤፍ ዱቄት ማቀነባበሪያ ፋብሪካን ጎበኙ።
በጉብኝቱ ወቅት የፋብሪካው ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወጣት ሐብታሙ በቀለ ፋብሪካው በሰዓት 16 ኩንታል ጤፍ መፍጨትና ማቀነባበር የሚችል አቅም እንዳለው ገልጸዋል።
ፋብሪካው ከ40 በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።
ወ/ሮ ሔለን ረታ በበኩላቸው፣ የግሉ ዘርፍ የምርት እሴትን በመጨመር፣ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ምርት በማቅረብ እንዲሁም ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ፊኒስ የጤፍ ዱቄት ማቀነባበሪያ ፋብሪካም በአጭር ጊዜ ያስመዘገበው ውጤት የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ፣ የግሉ ዘርፍ ተቋማት በምርት እሴት መጨመርና በወጭ ንግድ እንዲሁም በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት እንዲሰማሩ አስገንዝበዋል።


ፋብሪካው የተጣራና ጥራቱ የተረጋገጠ የጤፍ ዱቄት ለታላላቅ ሆቴሎች እያቀረበ ሲሆን በቀጣይም ምርቱን ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ዝግጅት እያደረገ ነው ተብሏል።
ከ8 ወራት በፊት ወደ ሥራ የገባው ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ከ10 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የራሱን የጤፍ እርሻ እያለማ መሆኑንና የግብዓት አቅሙን ለማስፋትም በተጨማሪ የእርሻ መሬት ላይ ለማምረትና አምራች አርሶ አደሮችን በመደገፍ እየሠራ መሆኑ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት የግሉ ዘርፍ አቅሙን እንዲያሳድግ፣ በተለይም በውጭ ንግድና በኢንቨስትመንት ዘርፎች በበለጠ እንዲሰማራ ለማገዝ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን በመስጠትና የገበያ ዕድሎችን በማመቻቸት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

