የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የረጅም ጊዜ ልማትን ለማረጋገጥ ሥትራቴጂ መሆኑን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የረጅም ጊዜ ልማትን ለማረጋገጥ ሥትራቴጂ መሆኑን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
በኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ዙሪያ ሀገራዊ የምክክር ፎረም በአዲስ አበባ ኮንቬንሽን ማእከል ተካሂዷል ።
በፎረሙም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር እና የብሔራዊ ድርድር ኮሚቴ ሰብሳቢና ዋና ተደራዳሪ ዶክተር ካሣሁን ጎፌ፣ ሚኒ ትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤትን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ዓለም አቀፍ የገበያ መዳረሻን ለማሥፋትና የንግድ እንቅፋቶችን ለማሥወገድ ከሚኖረው ሚና ባሻገር ፍትሃዊ፣ ተገማችና ደህንነቱ የተጠበቀ ዓለም አቀፍ ንግድ እንዲኖር ያሥችላል ብለዋል።

በድርድር ሂደቱ ኢትዮጵያ አስተማማኝ ቁመና ላይ ትገኛለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመንግሥት ሥራዎች ባለፈ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች ከዓለም አቀፍ ህጎችና አሠራሮች ጋር በመላመድ እንደ እሥካሁኑ ሁሉ የድርሻቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
“ኢትዮጵያን በንግድ በማስተሳስር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር” በሚል በተካሄድው ፎረም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር እና ዋና ተደራዳሪው ዶክተር ካሳሁን ጎፌ እሥካሁን የተካሄዱ የድርድር ሂደቶችን አንስተው አሁን ወሣኝ ምእራፍ ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ዲቪዥን ኃላፊ ማይካ ኦሺካዋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአባልነት ድርድር ሂደት አመርቂ ውጤቶችን እያሥመዘገበችና ለሌሎች በድርድር ላይ ላሉ ሀገራት አርዐያ በሚሆን መልኩ በወሣኝ ሂደት ላይ መሆኗን በፎረሙ ላይ ገልጸዋል።
በጉባኤውም የኢትዮጵያ የድርድር ሂደት እሥካሁን ምን ይመስል እንደነበርና አሁን የተደረሰበትን ደረጃ የሚያሣይ ሠነድ ቀርቧል።
የዓለም ንግድ ድርጅት 166 አባል ሀገራት ያሉት ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ 22 ሀገራት ደግሞ ለአባልነት በድርድር ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

