የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና ዋፋ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና ዋፋ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምቱን የተፈራረሙት የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ እና የዋፋ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ፋንታዬ ጌታነህ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎት ማስተዋወቅ፣ የአድቮኬሲ እና ምርምር እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስራዎችን በመስራት የግሉ ዘርፍ ድምጽ ለመሆን እየሰራ መሆኑን የገለጹን ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ ለንግዱ ማኅበረሰብ ምቹ የቢዝነስ ከባቢ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የቢዝነስ አካላት ጋር ለሚሰሩ ስራዎች ከዋፋ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ጋር በጋራ በመሆን በኩነት ዝግጅት፣ በፕሮሞሽንና ሀገራዊ ገጽታን በመገንባት ረገድ የተለያዩ ስራዎችን መስራት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
አንጋፋው የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለሚያከናውናቸው ሀገራዊ ታላላቅ ስራዎች ዋፋ ሰፊ ልምድና ተሞክሮ ያለው ተቋም በመሆኑ ትልቅ አጋር እንደሚሆን ጠቁመዋል ዋና ጸሐፊው፡፡
የዋፋ ምርኬቲንግና ፕሮሞሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ፋንታዬ ጌታነህ በበኩላቸው በሀገራዊ ገጽታ ግንባታ፣ በኩነት ዝግጅት፣ በማስታወቂያ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከምክር ቤቱ ጋር በቅርበት ለመስራት የላቀ ፍላጎት እንዳላቸው በስምምነቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡
ሁለቱም ተቋማት ሀገራዊ ምርትና አገልግሎትን ለማስተዋወቅና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በትብብር መስራት እንደሚገባቸውና ለዚህም የመግባቢያ ስምምነቱ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከሀገር ውስጥ ባለፈ በውጭ ሀገራት ለሚከናወኑ የተለያዩ ኩነት ዝግጅቶችም በትብብር እንደሚሰሩም በስምምነቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል ዋና ጸሐፊው ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ የዋፋ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽንን ወርክሾፕ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

