ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የንግዱ ማኀበረሠብ የላቀ ሚና እንደሚጫዎት ተጠቆመ።

ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የንግዱ ማኀበረሠብ የላቀ ሚና እንደሚጫዎት ተጠቆመ።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር “Business and Human rights” በሚል የተዘጋጀው ወርክሾፕ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱም የፍትህ ሚኒሥቴር ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና የንግዱ ማኀበረሠብ ተወካዮች ተገኝተዋል። በፍትህ ሚኒሥቴር የሰብዓዊ መብቶች ዳይሬክተር አቶ አወል ሱልጣን መሠል የውይይት መድረኮች የንግድ አሰራሮች ዓለም አቀፍ ሥታንዳርድ እንዲኖራቸውና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ለማድረግ ብሎም ውጤታማ ቢዝነስ መሥራት እንዲቻል አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መመሪያዎችም ግልጽ እንዲደረጉ በማድረግ ረገድ በፍትህ ሚኒሥቴር በኩል ከአንድ ሺ ሶስት መቶ በላይ መመሪያዎች ለማኀበረሠቡ ግልጽ እንዲሆኑ በሚኒስቴሩ ድረ-ገጽ ይፋ መሆናቸውን አንሥተው ይህም በአሠሪ እና በሠራተኛ ወይም በኃላፊ እና ሠራተኛ መካከል መመሪያን መሠረት ያደረገ ግንኙነት እንዲኖር ያሥችላል ብለዋል።
ከህጻናት ጉልበት ብዝበዛ፣ ህገ ወጥ የሠዎች ዝውውር፣ በኢንዱሥትሪዎች በሚሥተዋሉ የመብት ጥሰቶች እንዲሁም ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ትኩረት እንደተሠጣቸው አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት የህግና ግልግል ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሰላም ሰጠኝ በበኩላቸው የንግዱ ማኀበረሠብ በሚሠራቸው ሥራዎች የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማሥገባት ስታንዳርድ ያላቸውን ሥራዎች መስራት እንደሚገባና ምክር ቤቱም በጉዳዩ ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እንደሚሠራ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሶሺዮ ኢኮኖሚክ መብቶች ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ወይዘሪት ሐዊ አሥፋው በበኩላቸው የንግድ ተቋማት የሰብዓዊ መብት መርሆችን አክብረው መሥራት እንዲችሉ ለማድረግ ተከታታይነት ያላቸው የአቅም ግንባታ ሥራዎች እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

ተሣታፊዎችም በንግዱ ማኀበረሠብ እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መካከል ተከታታይ የምክክር ሥራዎች እንደሚያሥፈልጉ ገልጸው ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ህጎችም ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንዲሁም ከዳኒሽ ኢንስቲትዩት ፎር ሂውማን ራይትስ ጋር በጋራ በመሆን ከንግዱ ማህበረሠብ እንዲሁም ከቢዝነስና የሰብዓዊ መብቶች ጋር በተያያዘ በትብብር እንደሚሠሩ በመድረኩ ላይ ገልጸዋል።

