በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚገኙ የንግድና ዘርፍ ማህበራት አመራሮች በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና መሠረታዊ ፅንሰ ሀሳቦች ላይ የግንዛቤ መፍጠርያ ስልጠና



የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከGIZ-AU ጋር በመተባበር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚገኙ የንግድና ዘርፍ ማህበራት አመራሮች በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና መሠረታዊ ፅንሰ ሀሳቦች ላይ የግንዛቤ መፍጠርያ ስልጠና እየሰጠ ነዉ።
በስልጠናዉ መጀመርያ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሐጅ አህመድ ሃሊፋ የክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች ያለባቸዉን የአቅም ዉሱንነት ተረድቶ አቅማቸዉን ለመገንባት በአገር አቀፉ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እየተሰራ ያለዉ ስራ አበረታች ነዉ ብለዋል።
የኢትትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አመራሮች እየገባንበት ካለን አለም አቀፋዊና አህጉራዊ የንግድ ፉክክሮች አንፃር ለራሳቸዉ የተሻለ ግንዛቤ ኖሯቸዉ አባሎቻቸዉን ለፉክክሩ ማዘጋጀት አለባቸዉ ብለዋል።
አሁን ከአለም እራሳችንን ከልለን መቆየት የምንችልበት ሁኔታና ጊዜ ዉስጥ አይደለንም ያሉት ዶ/ር ቀነኒሳ አለም አንድ መንደር እየሆነች ባለችበትና የመጫወቻ ሜዳዉ ለሁሉም እኩል እስከተፈቀደ ድረስ ተፎካካሪ ለመሆን እራስን ማዘጋጀት ለነገ የሚባል አይደለም ብለዋል።
ከመክፈቻ ንግግራቸዉም ጋር አያይዘዉ ስለ ንግድ ምክር ቤቶች አመራር ዘይቤና አለም አቀፍ ተሞክሮም አቅርበዋል ዶ/ር ቀነኒሳ።
በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና መሠረታዊ ፅንሰ ሀሳቦች ላይ ስልጠና እየሰጡ ያሉት በGIZ AU የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካሪ የሆኑት አቶ ዉብሸት ካሳ ናቸዉ።

