አቶ ሰብስብ አባፍራ አባጆብርና ዋና ፀሐፊዉ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ከኢፌዴሪ የግብርና ሚንስቴር ሚንስትር ክቡር አቶ አዲሱ አረጋ ጋር በፅ/ቤታቸዉ ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰብስብ አባፍራ አባጆብርና ዋና ፀሐፊዉ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ምክር ቤቱ ከግብርና ሚንስቴር ጋር ተቀናጅቶ መስራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ከኢፌዴሪ የግብርና ሚንስቴር ሚንስትር ክቡር አቶ አዲሱ አረጋ ጋር በፅ/ቤታቸዉ ተወያይተዋል።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰብስብ አባፍራ አባጆቢር ስለ ምክር ቤቱ ዓላማና ተልዕኮ ለክቡር ሚንስትሩ በዝርዝር አስረድተዉ የግብርና ዘርፉ ከምክር ቤቱ ጋር ተቀናጅቶ መስራት ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ ያለዉ አዎንታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑንም አብራርተዋል።
የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ በበኩላቸዉ የግብርና ሚንስቴር ከምክር ቤቱ ባለድርሻ አካላት አንዱ መሆኑን በመጠቆም ከፊታችን ጥር 27 እስከ የካቲት 01 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የንግድ ምክር ቤቱ ለሚያዘጋጀዉ 15ኛዉ አለም አቀፍ ኢትዮ ቻምበር የንግድ ትርኢት ሚ/ር መስርያ ቤቱ ባለድርሻ አካላቱን እንዲያሳትፍም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢፌዴሪ ግብርና ሚንስቴር ሚንስትር ክቡር አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸዉ በግብርናዉ ክፍለ ኢኮኖሚ ተሰማርተዉ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች እሴት ሊጨምሩ ወደሚችሉ ዘርፎች በመሸጋገር ወደ ንግዱም እንዲገቡ ስለምንፈልግ ከምክር ቤቱ ጋር ተቀናጅተን ለመስራትና አስፈላጊዉን እገዛ ለማድረግም ዝግጁ ነን ብለዋል።
ምክር ቤቱ እያዘጋጀ ባለዉ 15ኛዉ አለም አቀፍ የኢትዮ ቻምበር የንግድ ትርኢት ላይም የግብርና ምርት አምራቾችና የግብርና ግብአት አቅራቢዎችን እንደሚያሳትፉም አሳዉቀዋል።

